የቀድሞ ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር, Facilitator for Change
አቶ ገላዬ ሃይሉ አየለ
የሕይወት ታሪክና የመታሰቢያ መልእክት
1956 – 2019 ዓ.ም.
የ Facilitator for Change ቤተሰብ የቀድሞ ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተራችንን አቶ ገላዬ ሃይሉ አየለን በሞት በማጣታችን ጥልቅ ሐዘናችንን እንገልጻለን። ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጆቻቸውና ለሁላችንም መጽናናትን እንመኛለን።
— የFC ቀድሞና የአሁኑ ሠራተኞችትውልድ
አቶ ገላዬ ሃይሉ አየለ ከአባታቸው ከአቶ ሃይሉ አየለ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ አሰገደች ተክለጊዮርጊስ ሕዳር 29 ቀን 1956 ዓ.ም. በሐረር ከተማ ተወለዱ።
ትምህርት
አቶ ገላዬ የመጀመሪያ እና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር ከተማ አጠናቀዋል። ከ1968 እስከ 1975 ዓ.ም. ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በልዑል ራስ መኮንን መቲሰቢያ አንደኛ ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ከ1976 እስከ 1980 ዓ.ም. ደግሞ በመድኃኔዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተምረዋል።
ከ1981 እስከ 1989 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ የትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል። በተጨማሪም በስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ በፕሮጀክት ዕቅድ ዝግጅት፣ በማኔጅመንት፣ በኮምፒዩተር እና በተለያዩ ሙያዊ መስኮች በተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት የሙያ ስልጠናዎችን ወስደዋል።
የሥራ ሕይወት እና ሙያዊ አገልግሎት
አቶ ገላዬ ሃይሉ አየለ በረጅም የሥራ ዘመናቸው በተለያዩ ተቋማት በማገልገል ሰፊ የሥራ ልምድ አካብተዋል።
የምክር አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ እና የማህበራዊ ዘርፍ ክፍል ኃላፊ
በሕፃናትና ወጣቶች ድጋፍና አገልግሎት ዘርፍ
የሕብረት ዘርፍ ክፍል ኃላፊ እና የጽ/ቤቱ ዋና አስተባባሪ
የሥነ-ልቦናና የሳይኮሶሻል አስተባባሪ፣ የደብረ ማርቆስ ፕሮጀክት አስተባባሪ
የፕሮግራም ኃላፊ እና ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር — የማይረሳ አስተዋፅኦ
በቅንነትና በታማኝነት ያገለገሉበት
ለሕፃናትና ለማህበረሰቦች ያበረከቱት አስተዋፅኦ
አቶ ገላዬ በረጅም የሥራ ዘመናቸው ከቤተሰቦቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች የተለዩ በርካታ ሕፃናትና ወጣቶችን በደብረ ማርቆስ፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ማዕከላት የምክር አገልግሎትና የተሃድሶ ስልጠና ድጋፍ አድርገዋል። በአገሪቱ ሰሜን፣ ምሥራቅ፣ ደቡብና ምዕራብ ክፍሎች በመንቀሳቀስ፣ በወቅቱ አስቸጋሪና ውስብስብ በነበሩ ሂደቶች ውስጥ በመሳተፍ፣ ሕፃናቱን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደገና ለማገናኘት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
በፋሲሊቴተር ፎር ቼንጅ በፕሮግራም ኃላፊነትና በሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተርነት በነበራቸው የአመራር ዘመን፣ በጥበብና በቁርጠኝነት ሠራተኞችን በማስተባበር ለበርካታ ደሃ እናቶች የኑሮ መሻሻል፣ ለአርሶ አደሮች በምግብ ሰብል ራሳቸውን እንዲችሉ እና በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ በርካታ ሺህ የጎዳና ሕፃናትና ወጣቶች የሕይወት ለውጥ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
የግል ባህሪያቸውና የሰው አገልግሎታቸው
አቶ ገላዬ ሃይሉ አየለ ለተቸገሩ ሕፃናትና ማህበረሰቦች ጥልቅ ሰብአዊ ርኅራኄ የነበራቸው፣ በጎ አድራጊና አሳቢ ሰው ነበሩ። በሥራ ባልደረቦቻቸው ዘንድም በሙያቸው፣ በትህትናቸው፣ በደግነታቸው እና ለድርጅቱና ለማህበረሰቡ ባበረከቱት በጎ አስተዋፅኦ ሁሌም በክብር ይታወሳሉ። በተጨማሪም ወላጅ ቤተሰቦቻቸውን ለረጅም ዓመታት በመርዳትና በመደገፍ ለብዙዎች አርአያ ነበሩ።
የመጨረሻ ዘመናቸው
በቅርቡ በደረሰባቸው ሕመም ምክንያት በሆስፒታልና በቤት የሕክምና እርዳታ ሲያገኙ ቆይተዋል። በዚህ ወቅት መላው የቀድሞና የአሁኑ የFC ሠራተኞች፣ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው፣ በተለይም የአዲስ አበባ ቤተሰብ፣ እስከመጨረሻው ደቂቃ ከጎናቸው በመሆን አስታምመዋቸዋል።
አቶ ገላዬ ሃይሉ አየለ በተወለዱ በ62 ዓመታቸው፣ በመስከረም 1 ቀን 2019 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። አቶ ገላዬ ሃይሉ አየለ አንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ።
አቶ ገላዬ ሃይሉ አየለን በክብር እናስታውሳለን።
ነፍሳቸው በሰላም ትረፍ።
